የፌዴራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት

ፌዴራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከ1961 ዓም ጀምሮ በሀገራችን በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ 57 ዓመት በስልጠና፣ በጥናትና ምርምር እና በማማከር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን እየሰራ ያለ ተጠሪነቱ ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሆነ አንጋፋ መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡
አመሰራረቱን ስንመለከት ኢንስቲትዩቱ በቱሪስት ድርጅት የቱሪዝም አማካሪ በሆኑት እስራኤላዊ ሚስተር ዴቪድ ኤፍራት አማካኝነት በ1961 ዓ.ም. መጨረሻ የሆቴልና ቱሪዝምሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በእንግዳ አቀባበል፣ በቤት አያያዝና በምግብና መጠጥ መስተንግዶ መሠረታዊ የአንድ ዓመት ሥልጠና መስጠት ጀመረ፡፡
በከመደበኛ ስልጠናው ባሻገር በየሆቴሎቹ ያሉትን ሠራተኞች የአጫጭር ጊዜ የሙያ ሥልጠና መስጠት፣ ታክሲ ነጂዎች እንግዶቹን ሲያስተናግዱ የቋንቋ ችሎታቸውን በማሻሻል ተገቢውን የእንግዳ እንክብካቤ እንዲያውቁ ሥልጠናዎችን ይሰጥ ነበር፡፡
በሆቴልና ቱሪዝም ዙሪያ የማያቋርጥ ጥናት ማካሄድም አንዱ የዓላማው ነበር፡፡ ተቋሙ አቅሙን በማሳደግ በሙያው መምህራን እንዲገነባ ከመደረጉም በላይ ቀጣይነት ባለው የከፍተኛ ትምህርት ስልጠና መምህራን እውቀታቸውን እንዲያሳድጉም እየተደረገ ይገኛል፡፡
በተቋማችን በሁለቱም የሙያ ዘርፎች እስካሁን የመደበኛና ተከታታይ ትምህርት ክፍል በየዓመቱ የሥራ ላይ ስልጠና የሚያገኙትን ሳያካትት ከ50 ሺህ በላይ ሰልጣኞችን አስመርቋል፡፡
የተግባር ትምህርትን በተመለከተ የሆቴል ሰልጣኞች በተግባር በተቋሙ ከሚያገኙት ሥልጠና ባሻገር በከተማው የሚገኙ ባለኮከብ ሆቴሎች የትብብር ስልጠና ያገኛሉ፡፡
የቱሪዝም ሰልጣኞች በቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎቻችን በሶስት አቅጣጫ ሙሉ መዳረሻዎቻችን ከመምህራን ጋር በመጎብኘት የተግባር ሥልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል፤ በተጨማሪም በአስጎብኝ ድርጅቶች አማካኝነት የትብብር ስልጠና ያገኛሉ፡፡
ተቋሙ በአሁኑ ጊዜ መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት መሰረት ያደረገ ስልጠና የሚሰጥባቸውን የሙያ መስኮች ደረጃ በማሳደግና በዘርፉ የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሚያስችሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ሌላው በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ኢንደስትሪውን በጥናትና ምርምር መደገፍ የሚያስችሉ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን በጥናትና ምርምር የሀገራችንን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ምግቦችን እያጠና በሆቴሎች የምግብ ዝርዝር ውስጥ እንዲገቡ እያደረገ ይገኛል፡፡
ከዩንቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የምርምር ኮንፈረንሶችን ያካሂዳል፤ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋርም የመግባቢያ ስምምነቶችን በመፈራረም በትብብር እየሰራ ይገኛል፡፡
በማማከርና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የሆስፒታሊቲ ኢንደስትሪው የሚፈልገውን ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል በባበለሙያ የተደገፈ የማማከር አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች ፣ለወጣቶችና ሴቶች ዘርፉን ያማከለ ስልጠና በመስጠት የሥራ እድል እንዲያገኙ ድጋፍ ያደርጋል፣ ከኢንደስትሪው ጋር ያገናኛል በራሳቸው ሥራ ፈጥረው እንዲሰሩም የቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
በሀገር ውስጥም በዘርፉ ስልጠና የሚሰጡ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችን የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎቻችን በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
መንግስት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማትን በአንድ አደረጃጀት እንዲመሩ ለማድረግ ተጠሪነቱን ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አድርጎ በአዲስ መልክ ሲያደራጀው ቱሪዝም ዘርፉን የሰለጠነ የሰው ኃይል ልማት ላይ በሰፊው እንዲሰራ ከማቀድ አንጻር መሆኑ ዕሙን ነው፡፡
ስለሆነም በቱሪዝም ዘርፍ ሀገራችን ካላት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህብ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርስ አንጻር ምንም ያልተሰራበት በመሆኑ ዘርፉን መደገፍና የሰለጠነና የበቃ የሰው ኃይል ማፍራት ልንመልሰው የሚገባን የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡
ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በአሁኑ ጊዜ የመንግስት አስተዳደር ሪፎርም ሥርዓትን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ለሥራ አመቺ የሆኑ መመሪያዎችን እና የአሰራር ማዕቀፎችን በራሱ ባለሙያዎች በማዘጋጀት ቀላል ቀልጣፋና ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶችን ለመከተል የሚያስችል ጅማሮዎችን እያስቀጠለ ነው፡፡
በሌላም በኩል የዓለም አቀፍ የአሰራር ደረጃዎችን ከማስረጽ አኳያም EOMS ISO- 21001፡2018 የምዘና ሂደቱን አጠናቆ እውቅና አግኝቷል፡፡
ከስልጠና ፍላጎት አኳያ የአጫጭር ስልጠና ከመቼውም በላይ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን በተለይ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመሄዱ እህቶቻችን ስልጠና በመስጠትና COC (ሲኦሲ) ምዘና እንዲወስዱ በማድረግ ዜጎቻችን የተሻለ የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የበኩሉን እየተወጣ ነው፡፡
ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ጊዜ በስምንት የሙያ መስኮች ሥልጠና የሚሰጥ ሲሆን በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የስልጠና መስኮች በአዲስ መልክ እየሰጠ ይገኛል፡፡
በዲግሪ፦ በሆቴል ማኔጅመንት
በቱሪዝም ማኔጅመንት
በኢቨንት ማኔጅመንት
በክሉናሪ አርት

በደረጃ ሶስትና አራት
1. በእንግዳ አቀባበል
2. በቤት አያያዝ
3. በምግብና መጠጥ ቁጥጥር
4. በምግብና መጠጥ መስተንግዶ
5. በኬክ ዝግጅት
6. በቱሪስት አስጎብኝ
በደረጃ አምስት

7. በክሉናሪ አርት(በምግብ ዝግጅት )
8. በቱርኦፕሬሽን
በቀጣይ ዓመታት በቱሪዝምና ሆቴል ዘርፍ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ይገኛል፡፡
በአጫጭር ስልጠና
 Hotel leadership management
 Hotel Supervision
 Culinary Leadership Management
 Hotel software IDS
 Wellness and SPA
 Nany (Local Domestic work )
በውጪ ቋንቋ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛና አረቢኛ ስልጠና እየሰጠ የሚገኝ በዘርፉ አንቱታን ያተረፉ ባለሙያዎችን ያፈራ ተቋም ነው፡፡
ለላቀ ብቃት እንተጋለን!
We Strive for Excellence